Isaiah 35

የተቤዠ ሕዝብ ደስታ

1ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤
በረሓው ሐሤት ያደርጋል፤ ይፈካል፤
እንደ አደይም ያብባል።
2በደስታና በዝማሬ ሐሤት ያደርጋል፤
የሊባኖስ ክብር ይሰጠዋል፤
የቀርሜሎስንና የሳሮንን ግርማ ይለብሳል።
የአምላካችንን ታላቅ ግርማ፣
የእግዚአብሔርን ክብር ያያሉ።

3የደከሙትን እጆች አበርቱ፤
የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ፤
4የሚፈራ ልብ ላላቸው እንዲህ በሉ፤
“በርቱ፤ አትፍሩ፤
አምላካችሁ ይመጣል፤
ሊበቀል ይመጣል፤
እርሱም ብድራቱን ይዞ፣
ሊያድናችሁ ይመጣል።”

5በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤
የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ።
6ዐንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፤
የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል፤
ውሃ ከበረሓ ይወጣል፤
ምንጮችም ከምድረ በዳ ይፈልቃሉ።
7ንዳዳማው ምድር ኵሬ ይሆናል፤
የተጠማው መሬት ውሃ ያመነጫል።
ቀበሮዎች በተኙባቸው ጕድጓዶች፣
ሣር፣ ሸንበቆና ደንገል ይበቅልበታል።

8በዚያ አውራ ጐዳና ይሆናል፤
“የተቀደሰ መንገድ” ተብሎ ይጠራል።
የረከሱ አይሄዱበትም፤
በመንገዱ ላይ ላሉት ብቻ ይሆናል፤
ገራገሮችም ከመንገዱ አይስቱም።
9አንበሳ አይኖርበትም፤
ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፤
እነዚህማ በዚያ ስፍራ አይገኙም፤
የዳኑት ብቻ በዚያ ይሄዳሉ፤
10 እግዚአብሔር የዋጃቸው ይመለሳሉ።
እየዘመሩ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤
ዘላለማዊ ደስታን እንደ አክሊል ይቀዳጁታል፤
ፍሥሓና ሐሤት ያገኛሉ፤
ሐዘንና ትካዜ ከዚያ ይሸሻሉ።
Copyright information for AmhNASV